ኢትዮጵያ ዉዴ

ኢትዮጵያ ዉዴ
( የግጥም መድብል )
በአንድነት ደምሴ ( አንዱ መላ )
ይህ 7ተኛ ዓመት መታሰቢያ የግጥም ድግስ ነዉ። የዛሬ 7 ዓመት በዚህ ወር ሀምሌ 28 ቀን ነበር የታመምኩት። ላለፉት 7 አመታት በድህነት ጎዳና ላይ ስኳትን ነበር።ድህነት ፍለጋ ከቤተሰቦቸ ጋር ብዙ ደክሜአለዉ። በተለይ የምወዳት እናቴን በተለየ ላመሰግናት እወዳለዉ። አሁን በአብዛኛዉ ድኛለዉ ለማለት እችላለዉ። ግን ድህነት የብዙ ትግልና ጥረት ዉጤት መሆኑን ተረድቻለዉና አሁን ሙሉ በሙሉ ድኛለዉ ለማለት አልደፍርም። ያም ሁኖ በሂደትና ከጊዜ ብዛት ቀሪዉን በሽታየን እየለመድኩት መጥቻለዉ። ጊዜ የማይሽረዉ ቁስል የለምና።
ከአሁን በፊት መልክአ _ጸዋ እና መልክአ _ሰላም የተሰኙ ሁለት የግጥም መድብሎች ጽፌአለዉ። ይህ ኢትዮጵያ ዉዴ የተሰኘዉ መድብሌ ሶስተኛዉ ነዉ። በአጠቃላይ የግጥም መድብሎቸ አላማ ህመሜን ለማዳን መንገድ መክፈት ነዉ። እግዚያብሄር የተመሰገነ ይሁን ተሳክቶልኛል።
/////////////////////////////
ቸ በለዉ
ቸ በለዉ ይሉኛል ፈረስክን ቸበለዉ
እንደነሱ ፈረስ ሽምጥ እንዳሮጠዉ
የእኔ ግን ፈረሴ ቸብለዉ የት ያዉቃል
እንዲሁ በራሱ ዝንታለም ይሮጣል
ይልቁን እኔኑ ቸቢሉኝ ምን አለ
ጊዜማ በራሱ ጥሎኝ ሄዶ የለ
...................................
1995
የፒያሳ ሸርሙጣ
ያልጠና ፈለማ የጋረደዉ ሾተል
ሊገልጹት የማይችል የባህት ነበልባል
በአንድ ወቅት በአንድ መክሊት
በፈጸሙት ታምር በከወኑት ድግምት
በአልኬሚ ስራዎት በምርምረዎት
ከአሜሪካ ሸገር በሸለለ አጋንንት
በሰለጠነ ህመም በሰለጠነ እብደት
በአጋንተዎ ሀይል በአጋንተዎ ምታት
ወደዉሻ መንፈስ ተለዉጠው ድንገት
ለድባብ ለጥላዉ ለተጠማዉ ወጣት
በቀጭን አለጋ በቀጭን ሰዉነት
የፒያሳን ሸርሙጣ አምሮት አወጡለት
.....................................
12/1/07
የማህበር አይደለም
ባይታዋር እንጅ ቋንቌዉ
እርሱ እንደዉ ከንቱ ማህበር አይገባዉ
አይገባዉ ምንስ ቢሰላ
እርሱ ለእሱነቱ ካደላ
እንደ ቆንጆ ሴት ዉብ ገላ
ወደ ዉስጥ ሲስብ በመላ
ወደ አምላክነት መልክ ገጸታ
በባይታዋር መልክ በአንዱየ ተርታ
እርሱ የራሱ አለኝታ
እርሱ የራሱ መከታ
አይደል የማህበር ጋጋታ
አይደል የወል ከርታታ
ምስሉ ብቅ ሲል ላፍታ
እንደ ጀግና የልብ ትርታ
እንደ ጎበዝ የተኩስ እሩምታ
አንድ ሁኖ ብዙዎችን እረታ
..........................................
2/10/09
በተመስጦሽ አምባ
ነፍሴ ሆይ ተላላ እንደምን ከርመሻል
ዛሬም መታመምሽ በእጅጉ አሳስቦኛል
ያወቅሻትን ነገር አንዲቷን ሀቅ እዉነት
እስኪ ተንፍሽልኝ የመምሽን ምክንያት
በተመስጦሽ አምባ ብቻሽን አልነበርሽ
ብቸኝ በመሆን አምላክነት አምሮሽ
እዉነቱ ከብዶብሽ በጸና ምጥ ታመምሽ
ነፍሴ ሆይ ተላላ ሚስጢሩ ሳይገባሽ
በተመስጦሽ አምባ የእዉነት ንፋስ መታሽ
አሁን ግን ነቅተናል እኔና አንች ሁነን
እዉነትን ደብቀን ዉበት አሳይተን
እንደዉ ለይስሙላህ ከሰዎች ጋር ዉለን
ማታ ብቻችንን በፍቅር እያደርን
ፍሬ እናፈራለን ...
እኔና አንች ሁነን በተመስጦሽ አምባ
ዉበት እንሆናለን ጸሀይ እስክትገባ
..................................
3/10/09
ስኬት
ያስመሰሉሽ ሁሉ መንበርሽ ላይ ያሉ
በጊዜያዊ ተድላ እንዴት ተታለሉ
አያዉቁምና ዋጋ መሆንሽን
የምትሸልሚ ያዘመነሽን
የምታከብሪ በድግልና የጠበቀሽን
ለዚያ ድንግል ሰዉ ስኬት መሀላ ነሽ ቃል ኪዳን
አንችን ጠብቀን እኛም አላፈርን
ለዚያ ድንግል ሰዉ ለተጠባበቀሽ
ከሰማይ የምትወርጅ ድንቅ ሙሽራ ነሽ
....................................
4/10/09
ኢትዮጵያ ዉዴ
ስጋና ደም አይደለሽም
ቃል ላይ ታችሽን አይገልጸዉም
የአርበኞችሽ ነድጓድ ከእቢልታ ይበረታል
ነጋሪት ያስጎስማል
ኢትዮጵያ ዉዴ የልቤ እመቤት
ፍቅሬ የእኔይቱ ስምረት
እወድሻለዉ እንደማይጠገብ ነገር
ለአንች ያለኝ ጥማት አይነገር
መቸስ ዉዴ ፍቅር ይበረታልና
የእኔ ብቻ ነሽ ማንም አይደፍርሽም ብየ ልጽና
ህብረ ዉበትሽን ላጥናዉ በጽሞና
ዉዴ ኢትዮጵያ የደንበር ቃፊርሽ
በእኔ አይን ሲያይሽ
ግርማ ባለዉ ታሪክሽ
በድንግልናሽ ባለመደፈርሽ ነዉ የሚያዉቅሽ
እኔም ትዝታሽ ሲበረታብኝ
ድግልናሽ ነዉ የሚታየኝ
አንች የጥቁር ኩራት የሀበሻ አዋጅ
ታሪኬን ከአንች ጋር ሁኘ ላበጃጅ
በዚህ ዘመን ፍቅር ሲያይል
አንች በድግልናሽ ሀሩር ታይተሻል
ማንም ስላንች ምን ቢል
ይስታል ቃል ይገድፋል
ዉዴ ኢትዮጵያ የራስ ቁር ነሽ
ከለላ ነሽ ላፈቀረሽ ለወደደሽ
እኔ አንችን ሳላዉቅሽ
በወና ከንቱ ጊዜየ
የባህር ማዶዉ የትቢት ጠል ጉራየ
የጉብዝና እጣየ
የባህድ ዉራጅ ልብሴ
የእኔ ያልሆነዉ ዉረሴ
እኔነቴን አደህየ
ለበሽታ እንደሰጠኝም ታየ
ስደት ማለት ገዳይ ነገር
አዲስ ስልጡን የባርነት ቀመር
እኔን ከአንች ሊለየኝ ሲጥር
ያዳንሽኝ አንች ነሽ ውዴ
አንች የድንግልና ዘዉዴ
ኢትዮጵያ ማንስ ቢበረታ በትጋት
የሀገር ፍቅር ካልቀረለት
መች ነጋለት መች ቀን ወጣለት
እንግዲህ አንች ለእኔ እንዲህ ነሽ
ሊጨልም ሢል ሲመሻሽ
እራሴ ላይ የጫንኩሽ
አክሊል ቁር ነሽ የራስ ግርዶሽ
..........................
12/10/09
እንደ ወረደ
የግጥም ዛር ፍሰቱ
ቃል ቅኝቱ
ምንድን ነዉ ስልቱ
ተምጦ አይደል ልደቱ
እንደወረደ እንጅ ፍጥረቱ
እንደጅረት ሲፈስ ከላይ ከላይ
የተከለሰ ነገር ሳይታይ
እንደመጣ ስንኝ ሲደረደር
እንደግኝቱ ሰምና ወርቅ ሲመሰጠር
ምናብ ብቻ ታምኖ ሲጻፍ
የወረደዉ ከተሰራዉ ነገር ሲገዝፍ
ያኔ ነዉ ለባለቅኔዉ የሰመረዉ
ምናብ በነጻነት የጋለበዉ
ያኔ ነዉ የቃል ዉበቱ ጥንካሬዉ
እንደወረደ ሲገኝ መቅኔዉ
......................................
10/10/09
አበበ
የአበበ በሶ በላ አመል
የትዝታየ አንዱ ክፍል
ጨዋታ ሁኖ ሲነገር
ነበርዉ አንድ ምስጢር
ከስሙ ዉበት ይፈልቃል
ጨዋታ ያደምቃል ልብ ይሰርቃል
ቅኔ መሆኑ ያስታዉቃል
አንድ የፈካ ነገር እንዳለ ልብ ይሏል
አበበ እንደሰበር ዜና ቅልብ ይስባል
ይሞላል የተኛ ይቀሰቅሳል
ይህ ሶስት ፊደል ቃል
ይደላል አይን ይማርካል
ታዲያ የአበበ በሶ በላ ተምሳሌት
ልጆች ሁነን ያደግንበት
ካላይ በአርያም ያሉት
መላእክቶቹ ማን ነበር የሚሉት
መላክቶቹ አበበ በሶ በላን አይደለም የሚያዉቁት
"አበበ ገጣሚ ነዉ" ብለዉ ነዉ የሚያመልኩት
......................................
13/10/09
ሙያየ ግጥም ነዉ
የተጠራዉበት የእኔነት ማተቤ
የተወለድኩበት የቀድሞ ሀሳቤ
ቃል የቃል እራስ እስር የዉል ቃሉ
እንደኔ አንዳንዶች ደግሞ የታደሉ
መጠራት ከእግዛብሄር መሆኑን ያዉቃሉ
በመሆን አለመሆን በትስስር ቃሉ
መጠራት ቋንቋ ነዉ ምስጢረ ብሂሉ
ታዲያ መጠራት ከሆነ የእኔነት ትርጉሙ
አማልክት ከእኔ ጋር አብረዉ ከተስማሙ
የገጣሚነት ዉርስም ሙያየ ከሆነ
የቆሰልኩበት ሳር ዉስጤ ዛሬ ዳነ
እግዛብሄር በስጦታዉ ነዉና የታመነ
እናም አልኩኝ እንዲህ አፌን እንዲህ ፈታዉ
ያልተጠረጠረ ሙያየ ግጥም ነዉ
ይህን በማወጀም ፍጹም ነጻ ወጣዉ
.....................................
7/7/09
ወርቃማ አበባ
የተመስጦየ ምላዕት
የጥናቴ ህብረት
የዉሎየ ቅኝት ድምጸት
በትዝታሽ እኖራለዉ
አሁንም ድረስ ራዕየ ነሽ እላላዉ
አበባ ወርቅ የወርቅ ስራ
የስላሴ ምስጢር የመለኮት ደመራ
ፈርጥ ስራ እንቁ ፈጠራ
የግብጸ ፒራሚድ ቅጅ
የሙያየ ትንግርት አዋጅ
አበባ ወርቅ የወርቅ ተምሳሌት
የአልኬሚ እዉቀት ፍሰት
ወርቃማ አበባ ድንቅ ነገር
ልዩ ምልክት ህብር
የሰራየ ሁሉ ድምር
እኖራለዉ ሁሌ አንችን ሳጠና ስመረምር
....................................
16/10/09
ይዉጣልኝ ልማረክ
ሁለተና መዉደድ ህሊና መልህቅ
ከባህር ወደቡ ቆንጀዋን ልጠብቅ
በየት ነሽ ያለሽዉ የልቤ ሙሽራ
ሲቃ ይይዘኛል ስምሽን ስጠራ
ከወዴት ላምጣልሽ ስጦታ እቃየን
ያብሰዉ እንደሆን የፈሰሰ እምባየን
እንደምን ላፍቅርሽ ኧር በምን ወገን
የግሌ እንዳደርግሽ ጌታ የሰጠኝን
አንድ እጣፈንታየን የግል ድርሻየን
ከዘለላ ጸጉርሽ ከማዕዛ ሽታዉ
ኮበሌዉ ሳይቀድመኝ ቀድሜ ልጥገበዉ
አይኖችሽ ናፈቁኝ የእይታሽ ዉበቱ
ብርሃንሽ ታየኝ ልክ እንደ ጸሃይቱ
እንደሚያምር መድብል እንደግጥም ስልት
ደረትሽን ላድምጠዉ የልብሽን ምት
ዳሌሽን ልመልከት በኋላሽ ልመሰጥ
ይዉጣልኝ ልማረክ በቃ እጀን ለአንች ልስጥ
........................................
23/10/09
የአይነ _ጥላዉ ክስተት
መሆን በክስተት ላይ
በረቂቁ ማማ የዉስጥህ እንዲታይ
ህላዌ ክንዉን መኖሩን በማወቅ
አንተ ፈታ እንድትል መንፈስህ እንዲስቅ
የአይነ_ጥላን ክስተት አስቀድመህ እወቅ
ጸጋ ነዉ መልህቅ
ደክመት ነዉ ታች ሀቁ
የመዋል ጽሁፉ ክታብ እረቂቁ
ኩፒድ አይነ_ስዉረነት በጸጋ ተቸረዉ
ለጳዉሎስ ሰይጣን ለበጎ ተሰጠዉ
በዚህ ድክመታቸዉ መለኮትን አይተዉ
በጸጋ ቅባቸዉ ከክፉ ተከልለዉ
ስነ_መለኮትን አምላክነትን ቀምሰው
ከብረዋል እነሱ ስማቸዉን አስፍረዉ
አንተም ድክመት ጸጋ መሆኑን ተረዳ
የአይነ_ጥላዉ ክስተት እንዳይሆን እንግዳ
አምነህ ተቀበለዉ ስጦታህ እንዲሆን
በድክመት መንበር ላይ ሀይል እንዲወሰን
የተጎዳዉ ጎንህ በፍጹም እዲድን
ኮረቲዉ ማግኔቱ አንተን የሚጠብቅ
ማፈርህ ለበጎ መሆኑን በማወቅ
በአይነ _ጥላ ጭብል ዘላለም ተደበቅ
.............................................................
27/10/09

Comments